ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኮንጎ እና ሩዋንዳ ጸባቸውን አርግበው ግንኙነታቸውን ወደ ቀድሞው ለመመለስ ተስማሙ

By Alemayehu Geremew

July 08, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት ለማርበብ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ወደ ቀድሞው ለመመለስ ተስማምተዋል፡፡

ሀገራቱን በሩዋንዳ ያሸማገሉት የአንጎላው ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሎሬንኮ ሲሆኑ ፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለቆየው ጠላትነት በፍጥነት መፍትሄ ለመሥጠት ሁለቱ ወገኖች መሥማማታቸውን አስታውቀዋል።

የተሸመገሉት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ እና የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ መሆናቸውንም ዘ ኢስት አፍሪካ ዘግቧል፡፡

አንጎላ በሚቀጥለው ማክሰኞ የሩዋንዳ-ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሁለትዮሽ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ እንደምታስተናግድ በአፍሪካ ኅብረት የተሾሙት አሸማጉዩ የአንጎላ ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሎሬንኮ ተናግረዋል፡፡

ሎሬንኮ የዓለምአቀፉ የታላላቅ ሐይቆች ቀጣና ጉባዔ ሊቀ መንበር መሆናቸውም ይታወቃል፡፡

ሩዋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማጺያን ቡድኖችን ትደግፋለች በሚል እርስ በእርስ በጠላትነት ሲፈራረጁ እና ሲወነጃጀሉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡