የሀገር ውስጥ ዜና

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሙከራ አገልግሎቱን በድሬዳዋ ሊጀምር ነው

By Shambel Mihret

July 07, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሙከራ አገልግሎቱን በድሬዳዋ ከተማ በቀጣዩ ወር እንደሚጀምር አስታውቋል።

ሳፋሪኮም በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ፥ በሐምሌ ወር የሲምካርድ ሽያጭን ጨምሮ የተለያዩ የኔትወርክ አግልግሎቶችን እንደሚያስጀምር እና እስከ ሚኒያዝያ 2015 ዓ.ም ድረስ ከ24 በላይ ከተሞች ላይ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ አመላክቷል፡፡

ተቋሙ ፈቃድ ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ የኔትወርክ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በማተኮር ታዎሮችን፣ ብሄራዊ የማሰራጫ ኔትወርኮችን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መዘርጋት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሰራ እንደቆየም ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ሙከራዎችን እያደረገ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ኩባንያው የኔትወርክ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉትን መገልገያዎች ከ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ወደ አገር ውስጥ እንዳስገባም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የቴሎኮም ኩባንያ የሆነው ሳፋሪኮም፥ አገልግሎቶቹን እያሰፋ የቴሌኮም ኩባንያዎች የሚሰጡትን አገልግሎች በጥራት ለመስጠት መዘጋጀቱንም አስታውቋል፡፡

በትግስት ብርሀኔ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!