የሀገር ውስጥ ዜና

የ2015 በጀት በ6 ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ

By Melaku Gedif

July 07, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2015 በጀት በስድስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ዛሬ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2015 በጀት ረቂቅ ላይ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ÷ በጀቱ በስድስት ጉዳዮች ላይ ማተኮሩን አብራርተዋል፡፡

የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎችም÷ ብድር መቀነስ፣ የበጀት ጉድለት መቀነስ፣ ያለንን ሀብት በቁጠባ መጠቀም፣ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ፣  መልሶ ማቋቋምና ሰብአዊ እርዳታ እና የሀገር ደህንነት እና ሰላምን ማስጠበቅ ናቸው፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ባይሠራ ኖሮ፥  ከአሁኑ የባሰ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በማብራሪያቸው ያነሱት፡፡

አሁንም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን ገልጸው÷ የመጀመሪያው ሥራም ጥብቅ የገንዘብ አስተዳደር መጠቀም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሁለተኛው ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን ጠቁመው÷ በግብርና ዘርፍ የተጀመረውን አስደማሚ ስራ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

ሌላው ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ የተጀመረው የልማት ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቁት፡፡

ባለፉት 11 ወራት ውስጥ 330 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበር አውስተው÷ 309 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰሰቡን ተናግረዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ጭማሬ ማሳየቱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማብራሪያቸው ያመላከቱት፡፡

ለዚህም ጠንካራ የገቢ ሰብሳቢ ባለሙያዎች እና ሙሉ በሙሉ ባይባልም የንግዱ ማህበረሰብ ግዴታውን ለመወጣት ያሳየው ቁርጠኝነት ውጤት ነው ብለዋል፡፡

ሀገራዊ እዳን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም÷ በዘንድሮው በጀት ዓመት ውስጥ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ ወይም ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ለብድር ክፍያ የተመደበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሀገራዊ ብድር በወቅቱ ሳይከፈል ከቆየ በጣም ከባድ ችግር ይዞ እንደሚመጣ አመላክተው÷ ከዘንድሮው በጀት ከፍተኛ ገንዘብ  ለብድር የሚከፈል ይሆናል ብለዋል፡፡