አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደምታጠናክር በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ገለጹ።
አምባሳደሩ 11ኛውን የደቡብ ሱዳን የነጻነት ቀን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አምባሳደሩ በመልዕክታቸው÷ወቅቱ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት ነው ብለዋል፡፡
የደቡብ ሱዳናዊያንን ከፍተኛ የሃይል ፍላጎትና አቅርቦትን ማሻሻልን ጨምሮ ሁለቱ እህትማማች ሃገሮች ለጋራ ብልጽግና እንደሚሰሩም አስረድተዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ከጥቂት ወራት በፊት የተፈረመው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ስምምነት ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን እና በሌሎች ዘርፎችም ላይ ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ሱዳን ፖስት ዘግቧል።