Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካን ቡድናቸው የኬንያ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬንያ ናይሮቢ የተካሄደው 39ኛው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል ሀገራት ርዕሳነ ብሔራት እና መሪዎች ጉባኤ ልዩ ልዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

በጉባኤው ላይ የተሳተፉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካን ቡድናቸው የናይሮቢ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ39ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ኬንያ፣ ናይሮቢ ማምራታቸው ይታወሳል፡፡

የኢጋድ የመሪዎች ልዩ ጉባኤም የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ግጭት ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማሳለጥ እና ለግጭቱ ሰላማዊ ዕልባት ለመስጠት የወሰዳቸውን አወንታዊ እርምጃዎች አድንቋል።

ይህንንም ጥረት ኢጋድ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ነው ያረጋገጠው።

የሱዳን የፖለቲካ ቀውስን ለመፍታትም በሱዳናውያን ባለቤትነት፣ በራሳቸው መሪነት የተጀመረውን ሁሉን አካታች ውይይት እና የመንግስት ውሳኔዎችንም አድንቋል።

በአፍሪካ ኀብረት፣ በኢጋድና በተመድ የሦስትዮሽ አመቻችነት በሱዳን ውስጥ የሚካሄደውን የሰላም ውይይት እንዲሁም በደቡብ ሱዳን በተደረሰው መሰረታዊ የሰላም ስምምነትና  ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ባቀረበው ጥሪ መሰረት ለሚደረጉት ጥረቶች ኢጋድ  ድጋፍፉን ገልጿል።

በ40 ዓመት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአካባቢው ያጋጠመውን የድርቅ አደጋ አስመልክተው መሪዎቹ የመከሩ ሲሆን፥ ለዚህ የተፈጥሮ አደጋ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አባል አገራት ተባብረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ያሰመሩበት።

የድርቅ አደጋው ከኮቪድ-19 እና ከከፍተኛ የጎርፍ አደጋዎች ጋር ተዳምሮ በቀጠናው የተፈጠረው ችግር በጉባኤው አጽንኦት ተሰጥቶታል ብሏል ጉባኤውን ተከትሎ የወጣው የጋራ መግለጫ።
 
እነዚህም ሁኔታዎች በቀጠናው የሰብዓዊና የጤና ችግሮችን ያባባሱ መሆናቸው ጠቅሶ፥ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ ለዓለም አቀፍ አጋሮች ጥሪ አቅርቧል።
Exit mobile version