አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የአሜሪካ ኤምባሲ ለዜጎች የሚሰጡትን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ ስለሚችሉበት ሁኔታ ዝርዝር ነጥቦች ተነስተዋል::
ሚኒስትር ዴኤታዋ በሚኒስቴሩ የሚሰጡ የተለያዩ የአገልግሎት አይነቶች ጊዜና ሁኔታን ከግምት በማስገባት ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እና ለሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች እየቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል::
በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለደንበኞች የሚቀርቡ የቪዛ አሰጣጥ ሂደቶችን ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን እና በሽግግር ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ጉድለቶችም በቅርቡ ይወገዳሉ ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የሚሰጡ የቆንስላ አገልግሎቶች የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ወዳጅነት ማዕከል ማድረግ እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
ሌሎች የሁለትዮሽ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን በሚመለከትም ሃሳብ በመለዋወጥ በቀጣይም ተባብሮ መስራት ለመንግስታቱና ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ያለውን ፋይዳ አስምረውበታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!