Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አገራዊ ምክክር ኮሚሸን ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችን አጠናቅቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባቱን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
ፕሮፌሰር መስፍን እንደገለጹት÷ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ኮሚሽኑን የማደራጀት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው÷ የድርጊት መርሐ ግብር በማውጣትም ወደ ዝግጅት ምዕራፍ የሚያስገቡ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡
በዝግጅት ምዕራፉም ለስራ የሚያስፈልገውን በጀትና ስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመው÷ በአጭር ጊዜ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸድቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
በዚሁ ምዕራፍ በአገራዊ ምክክሩ ሂደት የሚዘጋጁ የውይይት መድረኮችን የሚመሩና የሚያወያዩ ግለሰቦችንና ባለድርሻ አካላትን የመምረጥ፣ ስልጠና የመስጠት ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት ስለአገራዊ ምክክሩ ከአወያዮችና ተወያዮች ጋር በሚሰሩ ተግባራት ዙሪያ መግባባት ላይ በመድረስ ወደ ምክክር የሚገባበትን ምቹ መደላድል እንደሚፈጠር ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የዝግጅት ምዕራፉ በሚቀጥለው ዓመት የመጀመሪያ ወራት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመው÷ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀም በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ውይይትና ምክክር እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በውይይት ችግሮቻቸውን በማስወገድ ለቀጣዩ ትውልድ መልካም ውርስን ማስተላለፍ አለባቸው ነው ያሉት፡፡
በአገሪቱ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት እንዲረጋገጥና ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ወደ ወይይት መግባት አለበት ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version