አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ 2014 ዓ.ም የፊዚክስ እና የሂሳብ ትምህርት ተመራቂው ራጂ አሸናፊ 60 የትምህርት አይነቶችን A+ በማምጣት ታሪክ ሰርቷል፡፡
አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች ሲያሰለጥናቸው የቆዩ 1 ሺህ 253 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
የ25 አመቱ ወጣት ራጂ በአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮው አመት የፊዚክስ እና የሂሳብ ትምህርት ተመራቂ ሲሆን በ60 የትምህርት አይነቶች A+ በማምጣት አስገራሚ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
ራጂ ተወልዶ ያደገው ቄለም ወለጋ ጊዳሚ ከተማ ሲሆን የ10ኛ ክፍል ውጤቱ በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች A እንደነበር እና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤቱም 647 እንደነበር ተገልጿል፡፡
በዓለም ላይ ካሉት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባር ቀደም የሆነው ኤም አይ ቲ ራጂ እስከ ፒ ኤች ዲ ድረስ በዩኒቨርሲቲው ተቀላቅሎ እንዲማር ነጻ የትምህርት እድል ለመስጠት ቃል እንደገባላቸውም የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ተናግረዋል፡፡
በረጋሳ ፍሮምሳ