የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ምዕራብ ክልል የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ

By Alemayehu Geremew

July 02, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የክረምት ወራትየ በጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በቦንጋ ከተማ ተጀምሯል፡፡

መርሐ ግብሩን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ÷ በቦንጋ ከተማ መስቀል አደባባይ ቀጠና አዲስ ብርሃን ቁጥር አንድ መንደር ተገኝተው አስጀምረዋል፡፡

መረዳዳት የኢትዮጵያዊነት አንዱ መገለጫው ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ÷አቅም የሌላቸውን ዜጎች በመርዳት አጋርነታችንን ልናሳይ ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽኅፈት ቤት የ55 አቅመ ደካማ ሰዎችን ቤት እንደሚያድስ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡

በክልል ደረጃ በአጠቃላይ በዚህ ክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የ2 ሺህ 500 አቅመ ደካማ አረጋዊን ቤቶች እንደሚታደሱ ነው የተመላከተው፡፡

በክልሉ የቤት እድሳት፤ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና የጽዳት ሥራን ጨምሮ በ14 የሥራ መስኮች የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ እንደሚከናወም ተጠቁሟል፡፡

በተስፋየ ምሬሳ