Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን የቡና ምርት በአራት እጥፍ ያሳድጋል የተባለ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን የቡና ምርት አሁን ካለበት በአራት እጥፍ ያሳድጋል የተባለ የ15 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ይፋ አደረገ፡፡

የቡና ምርት ከ25 በመቶ በላይ ለሚሆነው ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መተዳደሪያ የሆነ ዘርፍ ስለመሆኑ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር ስትራቴጂው ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የቡና አመራረት ስልትን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ እሴት መጨመር፣ የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠርና ማዘመን እንዲሁም የተቋሙን አደረጃጀት እስከ ቀበሌ ድረስ ማደራጀትን ያካትታል ብለዋል።

በመሆኑም በዘርፉ አዳዲስ የአሰራር ሥርዓቶች ይዘረጋሉ፤ በእውቀት እንዲመራ የማድረግ እንዲሁም የተቋማዊ አደረጃጀት ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ነው ያሉት።

በዚህም በቀጣይ ዓመታት የቡና የውጭ ንግድ አሁን ካለበት 1 ነጥብ 196 ቢሊየን ዶላር ገቢ ወደ 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ስለሺ ጌታቸው ስትራቴጂው የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ ለ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን 470 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ 1 ነጥብ 26 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ለማድረስ እንደሚያግዝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version