Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ2015 በጀት ዓመት 100 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የከተማ አስተዳደሩ የ2015 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት የ100 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ።

ካቢኔው ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰበው በአጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ ከ2015 እስከ 2017 ዓመታትን ባካተተው የወጪ ማዕቀፍ ዕቅዱ ላይ የተወያየ ሲሆን፥ ለ2015 በጀት ዓመት በከተማው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ተዘጋጅቶ የቀረበውን የ100 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀትን ተቀብሎ እንዲፀድቅ ለከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ከረቂቅ በጀቱ ውስጥ 29 ነጥብ 79 ቢሊየን ብር ለክፍለ ከተሞች በድጎማ መልክ የሚሰጥ ሲሆን፥ ቀሪው 70 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ደግሞ በከተማው በማዕከል ደረጃ ለአስፈጻሚ አካላት የተበጀተ ነው፡፡

ከተያዘው በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት የሚውል የካፒታል በጀት ነው፡፡

ከተያዘው 70 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ውስጥ 54 ነጥብ 87 በመቶዉ የካፒታል በጀት ሲሆን፥ 42 ነጥብ 29 በመቶዉ ደግሞ ለመደበኛ ወጪዎች የሚውል ነው፡፡ ቀሪው 3 ነጥብ 87 በመቶ በመጠባበቂያነት የተያዘ በጀት መሆኑ በረቂቅ በጀቱ ላይ ተመላክቷል፡፡

ረቂቅ በጀቱ በከተማ አስተዳደሩ የተቀመጡ ግቦችን ውጤታማ ለማድረግ የመንግስት ሃብት ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው ዘርፎች መሰረተ ልማት፣ ለፈጠራ  እና ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ በመደልደል ሃብትን በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

Exit mobile version