Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” እና “ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን”

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርፃ እና አፅድቃ ወደ ስራ መግባቷ ተገለጸ፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያ የዲጂታል ዕድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል በኢትዮጵያ መንግስት የሚመራ ተነሳሽነት ነው፡፡
ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና የ10 ዓመት የልማት ዕቅድን ከመሳሰሉ ቁልፍ አገራዊ ስትራቴጂዎች ጋር እንዲሁም እንደ አፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ካሉ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና የልማት ኤጄንሲ ተዋንያንን በአንድ ላይ በማሰባሰብ፣ መሰረታዊ የዘርፍ ተነሳሽነትን በመለየት የአገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞን ለማሳለጥ እንዲሁም የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት የሚችሉና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ የሚችሉ አራት ስትራቴጂያዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎችን ለይቷል፡፡
ግብርና፣ የማምረቻ ዘርፍ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና ቱሪዝም ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች ናቸው።
ግብርና፡-
በግብርና ውስጥ የበይነ መረብ ቁሶች አርሶ አደሮች ምርታቸውን እንዲቆጣጠሩ ማስቻል፣ ጥብቅ ሰንሰለት ደግሞ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር፣ ደህንነቱ የተጠበቀና የተሻሉ (ርካሽ) የክፍያ አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችላቸው ማድረግ ነው፡፡
ኢትዮጵያን በዚህ ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ ሁለት ምቹ እድሎች ተለይተዋል፡፡
አንደኛው የዲጂታል ግብርና መድረክ መገንባት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቴክኖሎጂ መር የሆኑ የግብርና ኢንተርፕራይዞችን (ቴክ-ግብርና) መደገፍና ማበረታታት ናቸው፡፡
ማምረቻው ዘርፍ፡-
በዓለም አቀፍ ገበያዎች ተደራሽነትን ለማስፋት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አዳዲስ የግንኙነት ቴክኖሎጂዎችን መቀበል እና መፍጠር ማስቻል እና ኤክስፖርትን ለማሳደግ በዲጂታል የተደገፉ የሎጂስቲክስ አያያዝ አካሄዶችን ማጎልበት ናቸው፡፡
የመረጃ ቴክኖሎጂ፡-
በመረጃ ቴክኖሎጂ አስቻይ የሆነባቸው አገልግሎቶች መገንባትን ይመለከታል።
ከዚህ አማራጭ አንጻር ኢትዮጵያ ሁለት መልካም አጋጣሚዎች ተለይተዋል።
የመጀመሪያው ለባለ ከፍተኛ አቅም እና ተሰጥዖ ማዕከላት መሰረተ ልማት ማቅረብ ሲሆን÷ ሁለተኛው ደግሞ መሪ የንግድ ሥራ ሂደት አቅርቦትን ሊስቡ የሚችሉና ተሰጥኦ ማሳደጊያ የመረጃ ቴክኖሎጂ ፓርክን ዳግም በማዋቀር በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ማስገባት ናቸው።
ቱሪዝም፡-
ቱሪዝምን ተወዳዳሪ ለማድረግ የዲጂታል አሰራር መዝርጋት ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ሶስት መልካም አጋጣሚዎች ተለይተዋል።
የመጀመሪያው የቱሪዝም ዲጂታላይዛሽን ግብረ ኃይል በማቋቋም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ዲጂታላይዝ ማድረግ ሲሆን÷ ሁለተኛው ደግሞ የዲጂታል የገበያ ስርዓትን በማበጀት የቱሪስት ፍሰትን እና የቆይታ እና ተሳትፎ መጠኑን ማሻሻል ነው፡፡
ሶስተኛው ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የዲጂታል አገልግሎት እንዲሰጡ አቅም መገንባት ነው፡፡
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምንድነው?
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን÷ በአካል ከሚደረጉ ግንኙነቶች ወጥቶ የዲጂታል አሰራሮችን በመተግበር ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመድረስ ባለ ሂደት ውስጥ ያለ “ጉዞ” ነው።
የዲጂታል የሽግግር ጉዞ በመንግስት፣ በንግድ ድርጅቶች እና በማህበረሰቡ መካከል ግንኙነት በአካል ይካሄድ ከነበረበት አናሎግ ህብረተሰብ ወጥቶ ግንኙነትና ልውውጦች በበይነ መረብ በጣም ፈጣን፣ ርካሽ፣ እና ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወደ ሚካሄዱበት የተቀናጀና አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚደረግ ጉዞ ነው።
ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያመለክተው የተሻሻለ የኔትወርክ ግንኙነቶችን እና እርስበርስ ተያያዥነት ያላቸውን የዲጂታል መድረኮችን በመጠቀም የሚደረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ነው።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ከአናሎግ ኢኮኖሚ ይጀምራል። በአናሎግ ኢኮኖሚ ውስጥ በዜጎች በመንግስታና በንግድ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት የዲጂታል ቴክኖሎጂን የማይጠቀም እና በአካል የሚደረግ ነው።
ከአናሎክ ኢኮኖሚ ቀጥሎ የሚገኘው ደግሞ ዝቅተኛ የዲጂታል ተደራሽነት ነው። በዚህ ውስጥ ውስን የዲጂታል መሰረተ ልማት ይኖራል፤ የተወሰኑ የዲጂታል ማሳያዎች ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞው ይቀጥልና አናሎግ ግን የዲጂታል አሰራር እያደገ ይሄዳል። በዚህ ውስጥ አብዛኞቹ አገልግሎቶች አናሎግ የሆኑበት፣ ግልፅ የሆነ የዲጂታል ራዕይ ካልተቀናጁ አገልግሎቶች ጋር ያሉበት እና የሚተገበርበት ነው።
ይህ አናሎግ እና ያልተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት ደግሞ የተቀናጀ የዲጂታል ስርዓትን ይወልዳል።
በዚህ ውስጥ የላቀ፣ የተቀናጀ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትና ጠንካራ አስቻይ ስነ ምህዳሮች ይኖራሉ፡፡ የዲጂታል ኢኮኖሚም ይገነባል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ የተሟላ የዲጂታል ኢኮኖሚ የተተገበረበት፣ ከመንግስትና የንግድ ተቋማት ጋር ለመገናኘት የዲጂታል አገልግሎትን የሚጠቀም ነው፡፡ የንግድ ተቋማት ፈጠራ የታከለበት አገልግሎት ያቀርባሉ፡፡ የመንግስት ስራዎችና አገልግሎቶች ዲጂታል ይሆናሉ።
አብዛኞቹ የንግድ መነሻዎች ዲጂታል ይሆናሉ።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version