የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በአሸባሪው ቡድን የተዘረፉና የወደሙ የሕክምና ተቋማትን መደገፍ የሚያስችል ስምምነት ተደረገ

By Alemayehu Geremew

June 26, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ስምምነቱ የተካሄደው በሂውማን ብሪጅ፣ በሰዎች ለሰዎች ድርጅት፣ በወሎና ወልድያ ዩኒቨርስቲዎችና በአማራ ክልል ጤና ቢሮ መካከል ነው።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ዶክተር ኃላፊ መልካሙ አብቴ እንዳሉት የስምምነቱ ዋና ዓላማ በሽብር ቡድኑ ምክንያት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ማቋቋም ነው።

በሽብር ቡድኑ ምክንያት በርካታ የክልሉ የጤና ተቋማት መጠነ ሠፊ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሌሎች ድርጅቶችም ኾኑ ግለሰቦች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የሂውማን ብሪጅ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር አዳሙ አንለይ ድጋፍ ከመደረጉ በፊት በወደሙ አካባቢዎች በመገኘት የልየታ ተግባር መካሄዱን ጠቁመዋል።

በአሸባሪው ቡድን ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከውጭ ሀገር ተገዝተው የነበሩ የሕክምና ቁሳቁስ መዘረፋቸውንና መውደማቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፥ ሂዩማን ብሪጅ በጥናት ላይ ተመስርቶ የሕክምና ቁሳቁስ ከውጭ ሀገር እንደሚያስገባ ገልጸዋል።

የሰዎች ለሰዎች ፕሮፌሰር ፕሬዚዳንት እናውጋው መሐሪ በሽብር ቡድኑ ምክንያት የወደሙና የተዘረፉትን የጤና ተቋማት ለመገንባት ጠንክረው እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ስምምነቱ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ሲኾን እንደአስፈላጊነቱ ሊራዘም እንደሚችል የአሚኮ ዘገባ ያመላክታል።

በስምምነቱ መሰረት ሂውማን ብሪጅ ከስዊድን የሕክምና መሳሪያዎችን ያቀርባል፣ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የቀረቡ የሕክምና መሳሪያዎችን እስከ ጂቡቲ የሚያደርስ ሲሆን፥ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ድጋፍ ወደሚሹ የጤና ተቋማት ያደርሳሉ።