የሀገር ውስጥ ዜና

አሜሪካ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ላበረከተችው አስተዋጽኦ እውቅና ሰጠች

By Tibebu Kebede

October 25, 2019

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 13፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የዋሽንግተን ውጭ ህግ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ላለው አስተዋጽኦ የእውቅና ፕሮግራም አካሂደዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ሁለቱ ተቋማት ይህን ፕሮግራም ለኢትዮጵያ እውቅና ለመስጠት በማዘጋጀታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ይህም የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት አንዱ ማሳያ ነው ማለታቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሎም በሀገር ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም ጠቁመዋል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የህግ አማካሪ ማሪክ ስትሪንግ በበኩላቸው ፥ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት ከኤርትራ ጋር የነበረው የፖለቲካ አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ ማድረጓን አድንቀዋል።

ከዚህ ባለፈም በሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች መካካል ስምምነት እንዲደረስ፣ በኤርትራና በጅቡቲ፣ በሶማሊያና በኬንያ መካከል ያሉት አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ለተጫወተችው የመሪነት ሚና የእውቅና ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የ2019 የሰላም የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ይህም በሀገር ውስጥ ብሎም በቀጠናው ለጀመሩት ዘላቂ ሰላምን የመገንባት ጥረት አቅም የሚፈጥር መሆኑ ነው የተናገሩት ።