ዓለምአቀፋዊ ዜና

በአፍሪካ የመጀመሪያው የክትባቶች ማምረቻ ፋብሪካ በሩዋንዳ ሊገነባ ነው

By Alemayehu Geremew

June 24, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ከታቀዱት ሦስት የክትባት ማምረቻ ፋብሪካዎች ውስጥ የመጀመሪያው በሩዋንዳ ኪጋሊ ሊገነባ ነው፡፡

የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና የባዮቴክ የጥናትና የክትባቶች ማበልጸጊያ ተቋም ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኡጉር ሳሂን ÷ በኪጋሊ የሚገኘውን የክትባት ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ ትናንት አስጀምረዋል።

የክትባት ማምረቻ ፋብሪካው እስከ ፈረንጆቹ 2024 መጀመሪያ ድረስ የኮቪድ-19 ፣ የወባ፣ የሳንባ ነቀርሳ እና የኤች አይ ቪን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካን እያጠቁ ያሉ በሽታዎች ክትባቶችን እንዲያመርት ዕቅድ መያዙ ተመልክቷል፡፡

የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ÷ የፕሮጀክቱ መጀመር ክትባት በፍትሃዊነት ለማዳረስ ታሪካዊ የምዕራፍ መጀመሪያ ነውም ማለታቸውን የዘገበው አፍሪካን ኒውስ ነው።