አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት እየተወሰደ ያለው የተጠናከረ ህግ የማስከበር እርምጃ ሕዝብ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት ያጸና መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።
ጠንካራ መንግስት ባልዳበረበትና ግጭትና በጥብጥ በነገሰበት የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቀውስ ኢትዮጵያን የገፈቱ ቀማሽ ለማድረግ ታሪካዊ ጠላቶችና ውስጣዊ ባንዳዎች ሌት ተቀን ሰርተዋል።
በተለይም በአሸባሪው ሕወሃትና ተላላኪዎች ተልዕኮ አስፈጻሚነት የተደራጁ የሽብር ቡድኖች በለወጡ ማግስት አገራዊ ቀውስና ትርምስ እንዲፈጠር ሲታትሩ መቆየታቸውን የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል።
ከፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ሐጂ አወል አርባ፣ አቶ መለስ አለሙ እና አቶ ሳዳት ነሻ አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ሲፈትኑ ከነበሩ ፈተናዎች ጀርባ የሕወሃትና ተላላኪዎች እጅ ነበረበት ብለዋል።
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ዝርፊያና ንብረት ውድመት፣ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶች፣ የንጹሃን ጥቃቶች በመፈጸም አሸባሪው ቡድን ቀደም ብሎ በዘረጋው ውስጣዊና ውጫዊ መረብ ዋናውን ድርሻ ወስዷል።
በዚህም ላለፉት ዓመታት በየጊዜው ተለምዷዊ የመሰሉ መልከ ብዙ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች እየተከሰቱ ህዝቡን ለሞት፣ ለንብረት ውድመትና መፈናቀል እንደዳረጉ ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል በኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ዘረፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እገታና ሌሎች ወንጀሎች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ከብልጽግና ፓርቲ ምስረታ በኋላ አንገብጋቢው ህዝባዊ ጥያቄ በአገሪቱ ሕግና ስርዓት እንዲከበር በመሆኑ፣ መንግስትና ፓርቲው በህዝብ ጥያቄ መሰረት በተወሰደው ሕግና ስርዓት የማስከበር እርምጃ ውጤታማ ስራዎች እንደተከናወኑ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ከአሸባሪው ሕወሃት ወረራ በኋላ በተፈጠሩና ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ስጋት የሆኑ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ላይ በተወሰደ እርምጃ ስርቆት፣ ዝርፊና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ መቀነሱን ተናግረዋል።
ከጸጥታ ሃይሉ የከዱ፣ ከማረሚያ ቤቶች ያመለጡ እና በነፍስ ግድያ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች በሕገ-ወጥ አደረጃጀቶች ውስጥ እንደነበሩበት ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደው እርምጃ የወረራቸውን ቦታዎች የማስለቅቅ እና ህዝቡን በተለቀቁ ቦታዎች አደረጃጀቱን እንዲያጠናክር በማድረግ የተሰራውንም ጠቅሰዋል።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በጸረ ሰላም ሃይሎች ላይ በተወሰደ እርምጃ ለዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት መረጋገጡን፣ በኑሮ ውድነት ጫናውን ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
በሕግ ማስከበር እርምጃው የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ፈተናዎች እፎይታ የሰጠ፣ በህዝብና መንግስት መካከል መተማመን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ህዝቡም ከጸጥታ ኃይሉ እና ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የተጠናከረ ትብብር ያደረገበት አጋጣሚ እንደነበር አንስተዋል።
የህዝብ ሰላምና ፀጥታ እየተመዘገበ ባለበት ሁኔታ ከሰሞኑ አሸባረው የሸኔ ቡድን ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ መግደሉን ጠቅሰው፥ ይህም የአሸባሪ ቡድኑን ቀቢጸ ተስፋ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
በአንድ አገር የልማት ስራ ሰላም ከሌለ እውን ስለማይሆን ሰላምና ጸጥታን የማረጋገጥ ጉዳይ በቀጣይም በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባላት ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።