የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደሩ መንግስት በሠላም ማሥፈን እና ልማት ላይ የተገበራቸውን ሥራዎች ለብሪታኒያ የፓርላማ አባላት አስረዱ

By Alemayehu Geremew

June 22, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የወሰዳቸውን እርምጃዎች በኢትዮጵያና በጂቡቲ ጉዳይ ላይ ለተቋቋመው የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት አስረድተዋል፡፡

አምባሳደር ተፈሪ ፥ ህወሓት ለሦስተኛ ዙር ወታደራዊ ጥቃት እየተዘጋጀ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

ህወሓት ጥቃቱን ለመፈጸም የተዘጋጀው ታዳጊ ሕጻናትን በመመልመል ጭምር መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገውም ነው የጠቆሙት፡፡

አምባሳደሩ ፥ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ራስን በምግብ ለመቻል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት ግን የሰብዓዊ ድጋፍ ማስፈለጉን ነው አጽንኦት ሠጥተው የተናገሩት።

የፓርላማ አባላቱ ፥ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን ፖለቲካዊ መሻሻል እና ሀገሪቷ የያዘችውን በምግብ እህል ራስን የመቻል መርሃ-ግብር ማድነቃቸው በመረጃው ተመላክቷል፡፡

የፓርላማ አባላቱ ኢትዮጵያን መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ እና የእንግሊዝ ባለሐብቶችም በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ መረጃ እንደሚሰጡም ነው የጠቆሙት፡፡