አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰው በማገት ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት፡፡
ተከሳሹ አቶ መክት ጠጋ የሚባል ሲሆን ፥ ክሱ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ታህሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት አካባቢ በሶሮቃ ንዑስ ወረዳ ማይ አጋም ቀበሌ ልዩ ቦታው አዲባሪያ እየተባለ ከሚጠራው ስፍራ ላይ ካልተያዙ ሁለት ግብረአበሮቹ ጋር ሆኖ በጦር መሳሪያ በማስፈራራት የግል ተበዳይ የሆኑትን አቶ እንኳየ ንጉሴ እና አቶ ሽባባው ማሞ የተባሉትን በኃይል አግቶ ወስዷል የሚል ነው።
ተከሳሹ ታጋቾችን ለተከታታይ 8 ቀናት አስሮ ካቆየ በኃላ በቀን 15/04/2014 ዓ.ም በግምት ከረፋዱ 4:00 ሰዓት ሲሆን ፥ ቆላዛና ቀበሌ አጓልዕ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ላይ ከአቶ ማሩ ቻሌ 23 ሺህ ብር እንዲሁም ከአቶ ወርቁ ደሳለኝ 20 ሺህ ብር በመቀበል ታጋቾቹን እንደለቀቃቸውም ነው የተገለጸው።
በመሆኑም የቀረበውን የምርመራ መዝገብ በመመርመር በ1996 ዓ.ም ተደንግጎ የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 60(ሐ)፣ 590(1) (ለ) እና 2(ሐ) የተመለከተውን በመተላለፍ በፈፀመው ሰውን በከባድ ሁኔታ መጥለፍ ወንጀል በሶሮቃ ንዑስ ወረዳ ዐቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት የወንጀል የስራ ሂደት ዐቃቤ ህግ አማካኝነት ተደራራቢ ክስ ተዘጋጅቶ ለሶሮቃ ወረዳ ንዑስ ፍርድ ቤት የወንጀል ዳኝነት አገልግሎት አስተዳደር የስራ ሂደት ቀርቧል፡፡
በዚህም ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረቡትን የሰው ማስረጃዎች መዝኖ ተከሳሹን ተከላከል ሲል ብይን የሰጠ ሲሆን ፥ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር ያቀረበ ቢሆንም በይዘቱ ግን በዐቃቤ ህግ ክስ እና ምስክሮች የቀረበበትን ፍሬ ነገር አልተከላከለም።
በዚህ መነሻ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር፣ የቀረበውን ክስ እና የሰው ማስረጃዎች ከተገቢው የህግ ድንጋጌ ጋር መርምሮ የዐቃቤ ህግ አስረጂዎች /ማስረጃ በተከሳሹ ላይ በሚገባ ያስረዱ በመሆኑ ከቀረበው ጭብጥ አንፃር ሚዛን የሚደፋ ሆኖ በመገኘቱ በተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠቱም ነው የታወቀው።
በግራ ቀኝ በኩል የቀረቡ የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያዎችን በቅጣት አወሳሰን መመሪያው መሠረት ታሳቢ በማድረግ ፍርድ ቤቱ በቀን 13/10/2014 ዓ.ም ባዋለው የወንጀል ችሎት ተከሳሽን ያርማል ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ያስተምራል ያስጠነቅቃል ያለውን ውሳኔ በ15 ዓመት ፅኑ እስራት አንዲቀጣ የሶሮቃ ንዑስ ወረዳ ዐቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን ከማዕከላዊ ጎንደር ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!