አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 450 በረራዎችን በማድረግና አንድ ሚሊየን 610 ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል በመጓዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና የሰጣቸውን 195 ሀገራት የጎበኘችው አፍሪካ- አሜሪካዊት እንስት አነጋጋሪ ሆናለች፡፡
ጀሲካ ናቦንጎ ትባላለች። በፈረንጆቹ ጥቅምት 6 ቀን 2019 ወደ ሲሸልስ ጉዞዋን በማድረግ ላይ እንዳለች ነው ለዚህ የጉዞ እቅድ እራሷን ማዘጋጀት የጀመረችው።
በዓለም ሁሉም ሀገራት ከተጓዙ በጣም ጥቂት ሰዎች መካከል አንዷ መሆን ብቻ ሳይሆን እነዚህን ሁሉ ሀገራት በመጎብኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር በመሆንዋም ትጠቀሳለች።
በዚህም 450 በረራዎችን በማድረግና አንድ ሚሊየን 610 ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል በመጓዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና የሰጣቸውን 195 ሀገራትን ጎብኝታለች፡፡
በመጨረሻ በረራዋን ልዩ ያደረገው ደግሞ ጉዞዋ በ28 ጓደኞቿ እና ቤተሰቦቿ መታጀቡ እንደሆነ ተገልጿል።
“ጉዞው በጣም አድካሚ ነበር” የምትለው ናቦንጎ፥ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ170 በላይ በረራዎችን ማድረጓን ተናግራለች። “በአድካሚነቱ የተነሳ ብዙ ጊዜ ላቋርጥ አስብ ነበር” ስትል የሂደቱን ፈታኝነት ትገልጻለች።
ናቦንጎ ዓለምን ስትቃኝ ያጋጠሟትን ሁነቶች “ከቻላችሁ ድረሱብኝ “ የሚል ዓይነት ትርጉም ያለው “ዘ ካች ሚ ኢፍ ዩ ካን” በሚል ርዕስ መጽሐፍም ከትባ በፈረንጆቹ ሰኔ 14 ለአንባብያን አበርክታለች።
ይህን የጉዞ ታሪክ ለማድረግ ከአስር ዓመታት በፊት የምትጓጓለት እንደነበርም ነው የምትገልጸው።
መጽሐፏን ለመጻፍ የተገደደችባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች ስትገልጽም ፥ “ በዓለም ላይ ያሉትን ሁሉንም ሀገራት ጎብኝተዋል ተብለው ከሚታሰቡ 400 ወይም ከዚያ በላይ ተጓዦች መካከል ጥቁሮች ጥቂት ናቸው ስለሚባልም ነው” ትላለች፡፡
ይህ ታሪካዊ ጉዞዋ፥ ስለሰው ልጅ ያላት አመለካከት ላይ ልዩነት እንዳመጣላትም ከሲ ኤን ኤን ጋር በነበራት ቆይታ ገልጻለች፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!