Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በምዕራብ ኦሮሚያ የኦነግ ሸኔ አባላት እየፈጸሙት ያለውን ህገ ወጥ ድርጊት ለማስቆም የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የክልሉ ፖሊስ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ ዞኖች ውስጥ የኦነግ ሸኔ አባላት እየፈጸሙት ያለውን ህገ ወጥ ድርጊት ለማስቆም ከምን ጊዜውም በላይ የተጠናከረ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን በስፍራው እየተወሰደ ያለውን እርምጃ አስመልክቶ ዛሬ  በሰጡት መግለጫ ላይ መንግስት ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ የተደራጀ የህግ የበላይነት ማስከበርን ያለመ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው  የኦነግ ሸኔ አባላት በአካባቢው ላይ በንፁሃን ዜጎች፣ በፖሊስ አባላት እና በውጭ ሀገራት ዜጎች ላይ ግድያ መፈፀማቸውን ነው ያነሱት።

ከዚህ ባለፈም አባላቱ እያደረሱት ባለው ጥፋት በርካታ ንፁሃን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንም አመልክተዋል።

በሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በርከት ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም በመፈፀም ላይ ይገኛሉም ብለዋል።

ፖሊስ እስካሁን እየወሰደ ያለው እርምጃ አባላቱ ከፈፀሙት ድርጊት ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነ ዝቅተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።

አሁን ላይ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የክልሉ ፖሊስ ከአካባቢው ህብረተሰብ ፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን በቅንጅት የተጠናከረ እና የተደራጀ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል ብለዋል።

የኦነግ ሸኔ አባላትን በሎጀስቲክ እና በሌላ መልኩ ድጋፍ እየደረጉ ያሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች መኖራቸውን በመግለፅም እነዚህ አካላትን በተመለከተ ፖሊስ ጥናት እያደረገ መሆኑንና  የጥናቱን ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ነው የገለፁት።

 

በጥበበስላሴ ጀምበሩ

Exit mobile version