አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከአዲስ አበባ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በቀጣይ የአዲስ አበባ ከተማ ታክሲ ተራ አስከባሪዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተቀራርበው በሚሰሩባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል።
የታክሲ ተራ አስከባሪዎቹ በትራንስፖርት አሰጣጥ ላይ፣ በታሪፍና ስምሪት፣ ባለው የፓርኪንግ ችግር እንዲሁም ሌሎች በስራ ቦታ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል።
የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ የደም ልገሳ በማድረግ፣ በክረምት ችግኝ በመትከል፣ በጽዳት ዘመቻ ላይ በመሳተፍ እንዲሁም የአከባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ረገድ የታክሲ ተራ አስከባሪዎቹ እያደረጉት ላለው ተሳትፎ ኢንጂነር ታከለ ምስጋና አቅርበዋል።
የታክሲ ተራ አስከባሪዎቹ ከየትኛውም አካል በላይ ያልተገደበ አገልግሎት ለከተማዋ ነዋሪዎች እየሰጡ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፥ በከተማዋ ውስጥ በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ላይ እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
በቀጣይ የተለያዩ መዋቅሮችንና አሰራሮችን በመዘርጋት የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ያነሷቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አዲስ አበባን የመለወጥ ጉዞ የጀመርነው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ነዎሪዎች ትኩረት በመስጠት ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ፥ በከተማዋ ውስጥ አንድም የማይመለስ የነዋሪዎች ጥያቄ እንደማይኖርም አንስተዋል።