Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በነቀምቴ ዛሬ ከሰዓት በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተከስቶ በነበረ የእሳት አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  በነቀምቴ ከተማ በኬጀሞ በተባለ መንደር ዛሬ ከሰዓት በኋላ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተከስቶ በነበረ የእሳት አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ከባድ የቃጠሎ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የከተማዋ ፖሊስ ፅህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ማርቆስ ዋጋሪ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ የዕሳት አደጋው ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ላይ ነው የደረሰው።

ፖሊስ የእሳት አደጋው መነሻ ምናልባትም የኤሌከትሪክ  መቀጣጠል ሊሆን እንደሚችል መገመቱን እና ነገር ግን በቤት ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ቤንዚን ቃጠሎውን እንዳባባሰው ነው የጠቆሙት።

በዚህ አደጋ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፥ የአካባቢው ነዋሪ እሳቱን ለማጥፋት ባደረገው ርብርብ የሁለት ሰዎችን ህይወት መታደግ መቻሉን ተናግረዋል።

እነዚህም ሰዎች በአሁኑ ወቅት በነቀምቴ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ባለፈው ሳምንትም በምስራቅ ወለጋ ዞን ሲቡ ስሬ ወረዳ ስሬ ከተማ በደረሰ መሰል የእሳት አደጋ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።

ፖሊስ ህብረተሰቡ ቤንዚንን የመሰሉ ተቀጣጣይ ነገሮችን በመኖሪያ ቤት ውስጥ ከማስቀመጥ እንዲቆጠብ እና ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።

Exit mobile version