አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዩ ይልማ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለዉ አነጋገሩ።
አምባሳደር ተስፋዬ በመንግስት በኩል እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ገለፃ አድርገዉላቸዋል ።
በአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የቆየ ግንኙነት መኖሩን እና ይህ ግንኙነት ደግሞ እስካሁን ድረስ በተለያዩ መስኮች ትብብሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን በማስታወስ፥ በመንግስት በኩል ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያለዉን ግንኘነት በአዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ፍላጉት እንዳለው ጠቅሰዋል።
የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የመጠበቅ ሀላፊነት የመንግስት ዋነኛ ተግባር መሆኑን ገልፀዉ፥ የህወሓት ቡድን ከጎረቤት አገራት ላይ የሚያሳየዉ ጠብ ጫሪ ባህሪያት እንዲሁም ከአጎራባች ክልሎች ላይ የሚያደርገው ትንኮሳ በሰላም ጥረቱ ላይ አሉታዊ ተዕጽኖ እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሰላም እንዲሰፍን በተለያዩ አካላት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት የኢሰመኮ የተመድ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ጥምር የሰብዓዊ መብት ምርመራ ቡድን ባቀረበው ሪፖርት መሰረት ህጋዊ ማስተካከያዎች እና እርምጃዎች ማድረጉን አስተውሰዋል።
በተጨማሪም የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የጀመሩት የሰላም ጥረት እንዲሳካ ሙሉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
አምባሳደር ተስፋዬ ህወሓት በየጊዜዉ የሚያሳየው ቀጥተኛ ያልሆነ ፍላጎት እና ተለዋዋጭ ባህሪ የሰላም ጥረቱን እያስተጓጎለዉ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን በመንግሥት በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንዳስደሰታቸው በመግለፅ በሁለቱ አገራት መካከል ያለዉ የሁለትዮሽ እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአሜሪካ መንግስት ዘላቂ ሰላም በኢትዮጵያ እንዲኖር ፍላጎት እንዳለዉ ጠቅሰዉ ይህንንም ጥረት ኢትዮጵያ እንደምታሳካዉ እምነት እንዳላቸዉ ገልፀዋል ።
ብሄራዊ ውይይት ለማካሄድ ኮሚሽን መቋቋሙ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ እና አቅርቦት ለዜጎች እየደረሰ መሆኑ በበጎ የሚታይ እና የሚበረታታ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስዩ ይልማ ለአፍሪካ እድገት ነፃ የንግድ ዕድል የሚሰጠው (አጎዋ) ተጠቃሚነት ለኢትዮጵያ መሰረዟ በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስጋት መፍጠሩን ተናግረዋል ፡፡
የአጎዋን ስምምነት መሰረት በማድረግ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን ከቀረጥ ነፃ በማድረግ በአሜሪካ ገበያ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት የሚገያኙትን ጥቅም ለኢትዮጵያ እንዲፈቀድ እና እንዲታደስ ጠይቀዋል ።
አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን አሁን ያሉ የመንግስት በጎ እርጃዎች እና ለዉጦችን መሰረት በማድረግ በአሜሪካ መንግስት በኩል ተስፋ እንዳለ ተናግረዋል።
ተቋርጦ የነበረው የአጎዋ እድል በድጋሚ በአዲስ ሁኔታ የሚታይበት እድል እንዳለ ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።