Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ መንግስት የተላለፈው ሰብዓዊነትን ማዕከል ያደረገ የግጭት ማቆም ውሳኔ ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል- የዓለም ምግብ ፕሮግራም

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ መንግስት የተላለፈው ሰብዓዊነትን ማዕከል ያደረገ የግጭት ማቆም ውሳኔ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሊ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ባጠናቀቁበት ወቅት እንደገለጹት÷ ባለፉት ሁለት ወራት 2 ሺህ 500 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው መጋቢት ወር ለሰብዓዊነት ሲል ግጭትን ለማቆም ከወሰነ በኋላ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች እርዳታ እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ግጭትን አቁሞ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የታደገ በመሆኑ በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አድናቆት እንደተቸረውም ነው ያነሱት።

በሌላ በኩል በድርቅ የተጎዳውን የሶማሌ ክልል መጎብኘታቸውንም ጠቅሰው÷ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ግጭት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ችግር አባብሶታል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ።

በአገሪቱ የተለያዩ ችግሮች በመከሰታቸው በበርካታ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የእለት ደራሽ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰው÷ ከዚህ አኳያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር አንጻር ቀድሞ ሲያከፋፍል የነበረውን ድጋፍ ለመቀነስ መገደዱን አንስተዋል።

ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ መግለጻቸውንም ነው ኢዜአ የዘገበው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ተደጋጋሚ ድርቅና የአየር ንብረት ለውጥ በርካታ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ እንዲሆኑ አድርጓል ያሉት ደግሞ÷ የስዊዲን ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማቲልዳ ኤርንካራንስ ናቸው።

መንግስታቸው ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመው÷ ስዊድን በኢትዮጵያ የምትተገብረውን የአምስት ዓመት የልማት ስትራቴጂ እንዳዘጋጀች ነው የገለጹት።

የልማት ስትራቴጂው በየዓመቱ የ35 ሚሊየን ዶላር በጀት ያለው ድጋፍ እንዳካተተም ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version