Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በደቡብ ክልል ባለፉት 11 ወራት ከ11 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ባለፉት 11 ወራት ከ11 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም እንደገለጹት÷ በበጀት ዓመቱ 13 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን÷ ባለፉት 11 ወራት ከመደበኛ እና ከማዘጋጃ ቤት ከ11 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በኦዲት ፣ የግብር ከፋዩን ማህደር በመመርመር የተገኙ የአሰራር ግድፈቶችን ለማረም ጥረት የተደረገ ሲሆን የህግ ጥሰት በፈጸሙ ሰራተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

የገቢ አሰባሰቡ ከእቅዱ አንጻር የተሻለ አፈጻጸም ቢያሳይም ካለው የገቢ አሰባሰብ አቅም አንጻር የሚቀሩ ጉዳዮች መኖራቸውን ተገንዝበናል ብለዋል።

ከህግ ማስከበር ጋር በተያያዘ በፈጻሚው እና በግብር ከፋዩ ዘንድ የሚስተዋሉ የስነ ምግባር ጥሰቶችን በመለየት የእርምት እርምጃ ተወስዷል ያሉት ኃላፊዋ በተለይ ሀሰተኛ ደረሰኝ ማቅረብ እና ግብር መሰወር ላይ ያሉ ችግሮችን የማረም ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ከ1 ሺህ በላይ ሀሰተኛ ደረሰኝ የተገኘ ሲሆን÷ ከ187 ሚሊየን ብር በላይ በህገ ወጥ መንገድ ግብይት እንደተፈጸመ መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ክልሉ በቀጣዩ 2015 በጀት ዓመት 15 ነጥብ 665 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱ ታውቋል፡፡

Exit mobile version