አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር ባሳለፍነው ግንቦት ወር ብቻ ከ26 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው አስታወቁ።
ሚኒስቴሩ ሊሰበስብ ካቀደው 27 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ውስጥ 26 ቢሊየን 902ሚሊየን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 97 ነጥብ 23 በመቶ ማሳካት መቻሉን ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
አፈጻፀሙ ከባለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የብር 8 ቢሊዮን 960 ሚሊየን ወይም የ28 ነጥብ 46 በመቶ እድገት እንዳለው የገለፁት ሚኒስትሩ፥ አፈፃፀሙ በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ የተመዘገበ በመሆኑ ውጤቱ እጅግ በጣም ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተሰበሰበው ገቢ ምንጭ ከአገር ውስጥ ታክስ 13 ቢሊዮን 663ሚሊየን ብር የሚሸፍን ሲሆን፥ ከውጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ ደግሞ 13 ቢሊዮን 238ሚሊየን ብር መሆኑ ነው የተመለከተው።
በዚህም መሰረት የአስራ አንድ ወራት 330 ቢሊዮን 980ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 309 ቢሊዮን 448 ሚሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፥ የ93.49 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቧል ነው ያሉት።
ይህ የ11 ወራት አፈጻጸም ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከ50 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።