አዲስ አበባ፣ሰኔ 3፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር መልስ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል።
ብሄራዊ ቡድኑ በሳምንታት ቆይታው በማላዊ 2 ለ 1 ቢሸነፍም ግብጽን 2 ለ 0 በማሸነፍ በግብ ክፍያ በልጦ የምድቡ አናት ላይ መቀመጥ ችሏል።
ዋሊያዎቹ ወደ አዲስ አበባ ከመመለሳቸው በፊት በማላዊዉ ካሙዙ ኤርፖርት የኢትዮጵያ የአየር መንገድ ያዘጋጀላቸውን የድል ኬክ በመቁረስ ጉዟቸውን ያደረጉ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊት ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል።
ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ ሲደርስ በባህል እና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ እና የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና ሠራተኞች አቀባበል ተደርጎለታል።
ለልዑካን ቡድኑ የአበባ ጉንጉን በማበርከት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትም ተላልፏል።
ዋሊያዎቹ በተለይም ከ1989 በኋላ በፍጹም የጨዋታ ብልጫ የአፍሪካ ዋንጫ የአምስት ጊዜ ሻምፒዮኗን ግብፅን ያሸነፉበት መንገድ በስፖርት ቤተሰቡ ውዳሴን አስገኝቶላቸዋል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ፊታውራሪነት የሚመራው ቡድኑ ያሳየውን ማራኪ እንቅስቃሴ አጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ በ2023 በኮትዲቯር አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የመሳተፍ እድሉ ከፍተኛ ነው።
በማጣሪያ ጨዋታዎች ብሄራዊ ቡድኑ ከዚህ ቀደም የነበረበትን የአጥቂ ችግር በመቅረፍ በሁለት ጨዋታ ሶሰት ጎል ማስቆጠር የቻለ ሲሆን የፊት መስመር አጥቂዎች መሰረታዊ ለውጥ በሳምንቱ ጨዋታ ጎልቶ መታየት ችሏል።
የአዳማ ከተማው አጥቂ ዳዋ ሆጤሳ ደግሞ በ7 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ካሜሩን እና በ5 ጊዜ ሻምፒዮኗ ግብፅ ጎል ያስቆጠረ ብቸኛ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች መሆን ችሏል።