Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሕገወጥ ደላሎች ከሀገር ለመውጣት ሞክረዋል የተባሉ ከ100 በላይ ሰዎች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ አስተዳደር በሕገ ወጥ ደላሎች ከሀገር ሊወጡ ነበር የተባሉ ከ100 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
በከተማ አስተዳደሩ የ3ኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ኮማንደር ደሳለኝ አበራ እንደገለጹት ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ ከተማዋ ለሱዳን ያላትን ቅርበት ለመጠቀም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወጣቶችን ከሀገር እናስወጣችኋለን ብለው በማታለል ያመጣሉ።
ሱዳን ድረስ በተለያየ መንገድ እስከሚያሻግሯቸውም ለዚህ ዓለማ በተከራዩዋቸው ቤቶች ሰብዓዊ መብታቸውን በመግፈፍ አጉረው እንደሚያቆዩም ነው የጠቆሙት።
ዛሬም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና ከኤርትራ ወደ ዱባይ እናሻግራችኋለን በሚል የሠበሠቧቸውን ወጣቶች በአንድ ቤት ውስጥ አስቀምጠው ብር አምጡ በሚል በሚያሠቃዩበት ወቅት አንደኛዋ ወጣት በማምለጥ ለፖሊስ በሰጠችው ጥቆማ 97 ሴት እና 14 ወንድ ወጣቶችን ፖሊስ መያዙን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በመንግስት ወጭ ከሀገር ትወጣላችሁ በሚል አታለው እንዳመጧቸው ጠቅሰው፥ ጎንደር ከደረሡ በኋላ ግን ከሠዎች ጋር እንዳይገናኙ በማድረግ ብር ከቤተሠቦቻቸው እንዲያመጡ ሲያስገድዷቸው እንደነበርም ጠቁመዋል።
ብር ላልተላከላቸውም ድብደባ ይፈጽምባቸው እንደነበር ያነሡት ወጣቶቹ ለአንድ ወር ያክል አሰቃቂ ድርጊት ተፈጽሞብናል ብለዋል።
ድርጊት ፈጻሚዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የከተማ አስተዳደሩ ህገ ወጥ መከላከል ግብረ ሃይል እየሠራ መሆኑን የሚያነሡት ኮማንደር ደሳለኝ ወጣቶቹን ወደ ቀያቸው ለመመለስም እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ወር በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 150 ወጣቶችን ወደ ቤተሠባቸው መመለሳቸውንና ስድስት በዚህ ተግባር ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑንም ነው ኃላፊው የገለጹት።
በበላይነህ ዘለዓለም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version