አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስተዋወቀበትን የገርጂ መኖሪያ መንደር ፕሮጀክት ግንባታን አጠናቆ ሊያስመርቅ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ፕሮጀክቱ አሉሙኒየም ፎርም ወርክ ቴክኖሎጂ” የተሰኘ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ያዋለ ሲሆን÷ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች ቴክኖሎጂውን በማላመድ ግንባታውን በፍጥነት ያከናወኑበት መሆኑም ተገልጿል፡፡
ቴክኖሎጂው የግንባታ ጥራትና ፍጥነትን የሚያቀላጥፍ ሲሆን፥ ኮርፖሬሽኑ ይህን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ በማዋል በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ አስር ወለል ያላቸውን 16 ህንጻዎች ያየዘ የመኖሪያ መንደር መገንባት ችሏል።
የመኖሪያ መንደሩ ዘመናዊ የደህንነት ጥብቃ ስርዓት የተገጠመለት፣ ከ800 በላይ መኪና ማቆም የሚያስችል ስፍራ፣ የጋራ መጠቀሚያ አዳራሽ፣ የተለያዩ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ ካፌና ሬስቶራንት፣ መናፈሻ፣ አምፊ ቴአትር፣ የልጆች መጫወቻና መዋኛ ገንዳን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።
የመኖሪያ መንደሩ ግንባታ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯልም ተብሏል፡፡
የገርጂ መኖሪያ መንደር ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅ ያስቻለ፣ ብቃት ያላቸው የመንግስት ፕሮጀክት መሪዎች የታዩበት፣ አሰሪ፣ የግንባታ አማካሪ እና ተቋራጮች ለአንድ ዓላማ በትብብር በመስራት ትልቅ ነገር እውን ማድረግ እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ በቀበና ሳይት ያስገነባቸውን ሁለት ባለ አስር ወለል ህንጻዎች ግንባታ ያጠናቀቀ ሲሆን÷ ፕሮጀክቱ ለንግድና መኖሪያ ቤት የሚውሉ ቤቶች ያሉት በ1 ሺህ 167 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ዘመናዊ ህንጻ ግንባታ ነው ተብሏል።