Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የጤና ሚኒስቴር ለትግራይ ክልል የሚያስፈልጉ መድሃኒት እና የህክምና ቁሳቁሶች መቅረብ መቀጠላቸውን አስታወቀ 

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶ ጋር በመሆን ለትግራይ ክልል የተቀናጀ የጤና እና የስነ ምግብ አገልግሎት ማቅረብ መቀጠሉን አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ ተቋማትን በማስተባበር አስፈላጊ የጤና ግብዓቶች ለክልሉ እየቀረቡ ነው ብሏል።

ለአብነትም ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 45 ሚሊየን ብር የሚያወጡ መድሃኒቶች እና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ለክልሉ ተልኳል ብሏል።

በተጨማሪም የዓለም ጤና ድርጅት ለ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ሰዎች ለሶስት ወራት የሚያገለግል የህክምና ቁሳቁሶች  እና የተመጣጠነ ምግብ ወደ ክልሉ መግባቱን ነው የጠቆመው።

እንደዚሁም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ለመሰረታዊ ጤና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶች እና ከ64 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የኮሌራ እና ወባ በሽታዎች መከላከያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የተመጣጠኑ ምግቦች ቀርበዋልም ብለዋል።

በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር በኩል ለግማሽ ሚሊየን ለሚጠጋ ህዝብ ለሶስት ወር የሚሆኑ ከ58 ሜትሪክ ቶን በላይ መድሃኒቶች እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በኩል ደግሞ 76 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቁስ መቅረቡ ተመልክቷል።

በተጨማሪም በመቀሌ የሚገኘው አይደር ሆስፒታል ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የጤና ሚኒስቴር ማደንዘዣን ጨምሮ የተለያዩ መድሃኒቶችን በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር እና በዓለም ጤና ድርጅት በኩል ለማድረስ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።

Exit mobile version