Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የክልሉን ባለአንድ የከተማ ማዕከል መሆንን የሁሉም ዕድገት ብቸኛ መነሻ አድርጎ አቋም መያዝ የሕዝብን አብሮነት ወደ ጎን የተወ አካሄድ ነው – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉን ባለአንድ የከተማ ማዕከል መሆንን የሁሉም ዕድገቶች ብቸኛ መነሻ አድርጎ አቋም መያዝ የክልሉን ሕዝብ አብሮነት በጥርጣሬ ላይ እንዲመሰረት የሚያደርግ፣ አብሮነትን ወደ ጎን የተወና ለእኔ ብቻ ካልሆነ የሚል አስተሳሰብ ነው ሲል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገለጸ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫውም÷ ባለ ብዙ ከተማ ማዕከልነት በክልሉ ባሉ ከተሞች የተሳትፎ እድልን የሚያሰፋ፣ በየከተሞቹ በሚኖሩ የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳድግ እንዲሁም የክልሉን ሕዝብ አንድነት የሚያጠናክር እና በትብብር ላይ የተመሰረተ ፍትሐዊ የከተሞች እድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አመላክቷል፡፡
ይሁን እንጅ ከዚህ በተቃራኒ÷ የክልሉን ባለአንድ የከተማ ማዕከል መሆንን የሁሉም ዕድገቶች ብቸኛ መነሻ ነጥብ አድርጎ አቋም መያዝ የክልሉን ሕዝብ አብሮነት በጥርጣሬ ላይ እንዲመሰረት የሚያደርግ፣ አብሮነትን ወደ ጎን የተወና ለእኔ ብቻ ካልሆነ የሚል አስተሳሰብ መሆኑን የክልሉ መንግስት እንደሚረዳ ተመላክቷል፡፡
ይህም አንዳንድ እኩይ ዓላማ ያላቸውና በሕዝብ መካከል መቃቃር እንዲፈጠር የሚሠሩ ኃይሎች አስተሳሰብ በጋራ ተግባብተንና ተስማምተን የመጣንበትን የጋራ አቋማችንን የሚሽር፣ በሕዝብ ይሁንታ የጸደቀዉን ሕገ መንግስታችንን ጭምር የሚጻረር ነው ብሏል መግለጫው፡፡
ቀደም ሲል በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ ሲጠይቅ የቆየው ሕዝብ÷ አሁን ላይ ብዙም ባልተራራቁ ከተሞች በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ የተያዘው አቋም በተግባር የሚገለጽበት ወቅት በመሆኑ ሕዝቡ በተባበረና በተናበበ መንገድ ድጋፉን እንዲያሳይ ተጠይቋል፡፡
የባለ ብዙ ማዕከላት ክልል በመሆን ሂደትም ለሌሎች ክልሎች ተሞክሮን በሚያበረክት፣ የሕዝቡን ለዘመናት የቆየ የመልማት ጥያቄ በተግባር ለመመለስ የሚያስችል እንዲሁም ሁሉም የክልሉ ሕዝብ የጋራ ተጠቃሚነትና አብሮ የማደግ ፍላጎትን የሚያጠናከር እንዲሆን አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን መግለጫው አመላክቷል፡፡ ለተግባራዊነቱም የክልሉ ሕዝብ ከክልሉ መንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል፡፡
አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችና በሐሰተኛ ስም የሚጽፉ ግለሰቦች ይህንን ጉዳይ ያልተገባ መልክ ለማስያዝና በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ በመንዛትና ብጥብጥ በመፍጠር ዓላማቸውን ለማሳካት ሳይታክቱ እየሠሩ መሆኑም ተገልጿል፡፡
እነዚህ አካላት አንድነት ከሚከፋፍል ድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ መንግሥት ሕግና አሠራርን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል መባሉን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version