አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ህልውናዋ እና ሉዓላዊነቷ አደጋ በተጋረጠበት ጊዜ ሁሉ ፖሊስ ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የፖሊስ አመራርና አባላት የምስጋናና የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላም ጊዜ በየሰፈሩ በጦርነት ጊዜ በየግንባሩ ሰላም ለማስጠበቅ ደፋ ቀና የሚለው የፌደራል ፖሊስ ከብዙ ድል በኋል ክብረ በአሉን ለማክበር እና ተቋማዊ ስራውን ለህዝብ ለማሳየት በቅቷል ብለዋል፡፡
“ለዚህም እንኳን ደስ አላችሁ ልንላቸው ይገባል” ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ህልውናዋ እና ሉዓላዊነቷ ለአደጋ በተጋረጠበት ጊዜ ሁሉ ፖሊስ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ነበር ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
ሰዎች ወደ መከራ እና ግጭት ሲገቡ የሰላምን ዋጋ ቢገነዘቡም ለእናንተ ተገቢውን ክብር እምብዛም ያልሰጠን ቢሆንም ሰላም የምናድረውና ሃገራችንን ለማበልፀግ የምንጥረው እናንተን ተማምነን ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ እና የሰላምና ደህንነት ተቋማት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ብልፅግና መሰረቱ ሰላም ስለሆነ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የብርሃንን ጥቅም የምናውቀው በጨለማ እንደሆነ ሁሉ የህግ አስከባሪዎችን ሚና የምናውቀው ሰላም እና ደህንነታችን አደጋ ላይ ሲወድቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የሰላምን ዋጋ ብንገነዘብና ብናውቅ ለአፍታም ቢሆን ወደ ግጭት አናመራም ብለዋል።
በፖሊሶች የከሸፉ ወንጀሎችን ሳይሆን ከፖሊሶች እይታ ያመለጡ ወንጀሎችን አግዝፎ የመመልከት ባህል አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ፖሊስ በየዘመናቱ፣ በየወራቱ እንዲሁም በየቀኑ ለእኛ ማይነግረው ወንጀሎች ያከሽፋል፤ ነገር ግን ያከሸፈውን፣ የለፋበትን ያላመሰገንን ወንጀል ሲፈፀም ጣታችንን ልንቀስርና ልንወቅሳቸው አይገባም ብለዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው