የሀገር ውስጥ ዜና

ፎርትስኪው ፊውቸር ኢንዱስትሪ የአረንጓዴ ሃይል አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ነዳጅና አሞኒያ ለማምረት ፍቃድ ተሰጠው

By Meseret Awoke

June 02, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፎርትስኪው ፊውቸር ኢንዱስትሪ የተሰኘው የአረንጓዴ ሀይል አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ነዳጅ (ግሪን ሃይድሮጂንና) አሞኒያ ለማምረት ፍቃድ ተሰጠው።

ባለቤትነቱ የአውስትራሊያ የሆነው ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ በአረንጓዴ ሃይል 25 ጊጋ ዋት ሃይል ለማምረት አቅዷል።

ዜሮ የካርበን ልቀት ያለው የሃይድሮጅን ሃይል ለማምረት ፍቃድ የወሰደው ኩባንያው በቀጣይ ፋብሪካ የመገንባት ስራ ያከናውናል ተብሏል።

በሸራተን አዲስ በተደረገው ይፋ የማድረግ መርሐ ግብር የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ፥ ኩባንያው ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ ሃይል የምታገኘውን ሃይል ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የፎርትስኪው ፊዩቸር ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጁሊ ሽትልዎርዝ በበኩላቸው ፥ ኩባንያው የአረንጓዴ ሃይልን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ሃይል የተመቸች መሆኗን ያነሱት ስራ አስፈጻሚዋ ፥ ኩባንያው እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ላደረገው የገንዘብ ሚኒስቴር ምስጋና አቅርበዋል።

የሀይድሮጅን አሞኒያ ሃይል በተለይም ተሽከርካሪዎችን ከተፈጥሮ ነዳጅ ውጪ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል እንደሆነም ተጠቅሷል።

ኩባንያው በቀጣይ ፋብሪካውን የመገንባት እንቅስቃሴ የሚጀምር ሲሆን ፥ ፋብሪካው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የሀይድሮጅን ሃይል አረንጓዴ ነዳጅ ወደ ውጭ የመላክ አቅም ይፈጥርላታል ተብሏል።

በታሪኩ ለገሰ