Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀገራት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጉዞ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀገራት እና አጋር አካላት ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለትውልድ የሚተላለፈውን አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ ጉዞ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስዊድን እና ኬንያ በጋራ ስቶኮልም ፕላስ 50 የተሠኘውን ኮንፈረንስ በማዘጋጀታቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለኮንፍረንሱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት የስቶኮልም ኮንፈረንስ ልማትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ያወዳጀ የመጀመሪያው ኮንፈረንስ እንደሆነ አንስተዋል።

በኮንፈረንሱ ድህነትን በተመለከተ የተነሱ ሃሳቦች ቦታ ተሰጥቷቸው መንሸራሸራቸውንም አድንቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሀገራት ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው መስተጋብር አካባቢን በማይጎዳ እና ዓለም አቀፉን የአካባቢ ጥበቃ ሥምምነት መርህዎች ባከበረ መልኩ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ጤናማ ዓለም እንዲኖረን ተባብረን በአንድነት በመቆም መሥራት ግድ ይለናልም ነው ያሉት፡፡

እያጋጠሙን ያሉትን ፈተናዎች ለመፍታት በበኩላችን ምን ተወጥተናል ? በቀጣይስ በሀገር እና በተቋም ደረጃ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ለመሥራት ምን አስበናል ? በሚሉት ጉዳዮች ላይ መሥራት ይኖርብናል ነው ያሉት።

ዓለም አቀፉን የአካባቢ ጥበቃ ሥምምነት መርህዎችንም አክብረን ለተግባራዊነቱ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በርካታ ሥራዎች መሥራቷንና አሁንም እየሠራች እንደምትገኝ ያነሱ ሲሆን፥ ለአብነትም በፈረንጆቹ 2019 ተግባራዊ መደረግ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ጠቅሰዋል።

በመርሃ-ግብሩ እስከ ፈረንጆቹ 2022፥ 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ በፈረንጆቹ 2021 18 ቢሊየን ችግኞች መትከል እንደተቻለ ያነሱ ሲሆን ÷ በዚህ ዓመት ችግኖችን መትከል ስንጀምር ደግሞ በአራት ዓመታት ውስጥ እናሳካለን ብለን ካቀድነው በላይ ችግኞች ከወዲሁ መትከል እንችላለን ብለዋል፡፡

ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ችግኖችን በመትከል የተወሰነ ሳይሆን ከሀገራት ጋር በመተባበር፣ በጋራ በመቆምና ፣ ችግኞችን በመካፈል ሌሎችም ተክለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተካፋይ እንዲሆኑ ያስቻለ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በቀጣይም ሀገራት የአካባቢ ጥበቃ እና የዓለማችንን ጤንነት ከመጠበቅ አንጻር ሃላፊነት ወስደው እንዲተገብሩ ኢትዮጵያ በጀመረችው የአረንጓዴው አሻራ የልማት ጉዞ ላይ ተካፋይ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ መተባበር እና በአንድነት ስለመቆም ያነሱትን ሃሳብ ሲያብራሩም ÷ ሁላችንም የአንድ ዓለም ህዝቦች እንደመሆናችን መጠን የሚከሰቱ ችግሮችም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሁላችንንም ያገኙናል ብለዋል፡፡

ለአብነትም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ሁላችንንም የፈተነና በአንድነት እና በትብብር እንድንቆም ያስቻለ አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም ሁሉንም ሀገራት ያካተተ፣ በዕውቀት ሽግግር እና በትምህርት ላይ የተመሠረተ መተጋገዝ ሊኖር እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version