Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያና አሜሪካ በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ትብብራቸው እንዲጠናከር እሠራለሁ- የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ትሬንት ኬሊ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና አሜሪካ በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ትብብራቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ትሬንት ኬሊ ገለፁ፡፡
የኮንግረስ አባል ትሬንት ኬሊ እና የልዑካን ቡድናቸው እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ዲጂታል ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸው ወቅት ኮንግረንስማን ትሬንት ኬሊ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያና አሜሪካ በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ በተለይም ደግሞ ሽብርተኝነትና ሌሎች ድንበር-ዘለል ወንጀሎችን በጋራ በመከላከል የቆየና የዳበረ አጋርነት አላቸው፡፡
ይሄው ትብብራቸውም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕከት÷ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቁመው፥ ሀገራቱ አሁንም በተለያዩ የትብብር መስኮች በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ጠንካራ የአሜሪካ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ገልጸው÷ ይህን አጋርነት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ተቋም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲሁም በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ያለውን ትብብር የበለጠ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በተደረገው ሪፎርም÷ አጋርነትና ትብብርን ማጠናከር፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በመሆን ሁሉንም እኩል የሚያገለግል ተቋም ማደራጀት፣ ስትራቴጂክ እይታ ያለው አመራር መገንባት፣ ፕሮፌሽናልና ኢትዮጵያን የሚመስል የሰው ኃይል ማብቃት እንዲሁም የዘመኑን የደኅንነት ስጋት የሚመክቱ የቴክኖሎጂ አቅሞችን ማልማትና መጠቀም መቻሉን አቶ ተመስገን አስረድተዋል፡፡
እስከ አሁን የተከናወኑት እነዚህ ተግባራትም አካባቢያዊና አህጉራዊ ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ በኩል መሰረት መሆናቸውን ገልጸው÷ በዚህ ረገድ የአሜሪካ አጋርነት ወሳኝ በመሆኑ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
ኮንግረንስማን ትሬንት ኬሊ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያና አሜሪካ እንደ ሽብርተኝነት ዓይነት ዓለምአቀፋዊ የደኅንነት ስጋቶችን ለመከላከል በጋራ እየሰሩ በመሆናቸው የሁለቱ ሀገራት የመረጃና ደኅንነት ተቋማት የጀመሩት ትብብርና አጋርነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ መግለፃቸውን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version