የሀገር ውስጥ ዜና

በአሶሳ ከተማ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሰረተ ልማት ለመዘርጋት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

By Shambel Mihret

May 31, 2022

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሶሳ ከተማ በሁለት ዓመት የሚጠናቀቅ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሰረተ ልማት መዘርጋት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በከተማዋ ያለውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት እጥረት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት የሚያስችለውን ፕሮጀክት ለማስጀመር የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በኤሌክትሪክ አገልግሎት የዲስትሪቡዩሽን መልሶ ግንባታ ኃላፊ አቶ ተፈራ ደርበው እንደገለጹት÷ ተቋሙ በተለያዩ ከተሞች ዘመናዊ የሆነ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በመገንባት ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ የሆነ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለማድረስ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

ተቋሙ ከዓለም ባንክ ባገኘው 100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በኢትዮጵያ በ11 ከተሞች ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት በዝግጅት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህ ከተሞች መካከል አሶሳ ከተማ አንዷ መሆኗን ጠቅሰው÷ ከ20 ዓመት በፊት በከተማዋ የተዘረጉ የእንጨት ምሰሶዎች እና ትራንስፎርመሮች እንዲሁም ኃይል ተሸካሚ ገመዶች በአዲስ መልክ ይዘረጋሉ ነው ያሉት፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት የአሶሳ ዲስትሪክት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ከበደ በበኩላቸው የሚዘረጉ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ከከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር የተቃኙ መሆናቸውን ገልጸው÷ በትግበራው ወቅት ማህበረሰቡ ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ይፋ የሆነው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅም በከተማዋ የሚስተዋለውን የኃይል መቆራረጥ እና እጥረት ከመፍታት ባሻገር በከተማዋ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ትልቅ ዕድል ይሰጣል ማለታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡