Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የኮሮና ቫይረስን ለመዋጋት ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በአጋርነት  እየሰሩ ነው

አዲስ አበባ፣የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር እየሰሩ ነው።

እርምጃው ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ እየተበራከቱ የመጡ ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ያለመ ነው ተብሏል።

ቲክ ቶክ የተባለው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ትክክለኛ መረጃን ለተጠቃሚዎቹ ለማድረስ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎም ባለፈው ሳምንት የዓለም ጤና ድርጅት ሰዎች እንዴት ራሳቸውንና ሌሎችን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያሳይ ቪዲዮን በቲክ ቶክ ላይ በመልቅቅ 27 ሚሊየን ሰዎች ተመልክተውታል።

የዓለም የጤና ድርጅት በበኩሉ ከተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ጋር መስራቱ ትክክለኛውን ተጠቃሚ ለማግኘትና ሰዎች በሚፈልጉበት ቦታ ሆነው ስለ በሽታው ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ያስችላል ብሏል።

ቫይረሱ ባለፈው ታህሳስ ወር በቻይና ከተከሰተ ወዲህ ያልተረጋገጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና ዜናዎች በቲክ ቶክ፣ ትዊተር እና ፌስቡክ እንዲሁም በቻይና ውስጥ በጣም ታዋቂ በሆኑት ዊአቦ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በሰፊው መሰራጨታቸው ተነግሯል።

ድርጅቱም ከቲክ ቶክ፣ ፌስቡክ እና ትዊተር ጋር ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመቆጣጠር አዲስ ስልት በመንደፍ የኮምፒውተር ደህንነት ጥበቃ ሶፍትዌር ለማበልጸግ እንደሚሰራ፥ ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም አረጋግጠዋል።

 

ምንጭ፦ ኒውስ ቱደይ

 

 

 

Exit mobile version