Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመጪው ክረምት ከባድ ዝናብ ስለሚኖር ከወዲሁ ከጎርፍ አደጋ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል- የሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው የክረምት ወቅት ጎርፍና መሰል አደጋዎች ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ስለሚኖር የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

ሰሞኑን የታየው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች የመጣ መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታና የአየር ጠባይ ትንበያ ባለሙያ ታምሩ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በቀጣዩ ክረምት ወቅት ከመደበኛው በላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ትንበያዎች ያመለክታል።

የላሊና የአየር ጠባይ ለውጥ ሳቢያ በአገሪቱ በበልግም ሆነ በመኸር ወቅቶች ደረቅ ወራት በዝተው መስተዋላቸውን የተናገሩት ባለሙያው፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ሐምሌና ነሐሴ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖር ይችላል ብለዋል።

በተለይም በአገሪቱ በሰሜን ምስራቅና በምስራቅ አካባቢዎች ላይ ዝናቡ እየጨመረ እንደሚሄድ ጠቁመዋል።

ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው ከፍተኛ የሙቀት መጠን የላሊኖ ተፅእኖ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጋር ተያያዥ በመሆኑ ለጎርፍ አደጋ ሥጋት እንደሚሆንም አብራርተዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ፥ የጎርፍ አደጋ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች የኅብረተሰብም ሆነ ተቋማት ከወዲሁ የአደጋ የመከላከል ሥራ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

በተለይ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ፣ በወንዞችና ተዳፋትማ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተጠናከረ የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በአገሪቱ የተከሰተው ላሊና የመኸርና በልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑት የቦረና፣ ባሌ፥ ሶማሌና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች በቂ ዝናብ እንዳያገኙ ምክንያት መሆኑንም ነው አስረድተዋል።

የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የግብርናና ሌሎች መሰል የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላሊኖ የሚፈጥረውን አደጋ ለመመከት ከወዲሁ አስፈላጊ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ከግንቦት ወር መጀመሪያ ጀምሮ የሙቀቱ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው በከተሞች መስፋፋትና የውኃ አካላት መመናመን ምክንያት መሆኑንም ነው ያነሱት።

ኅብረተሰቡም የተለያዩ ተክሎችን በመትከልና በመንከባከብ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ መቋቋም እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

Exit mobile version