Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመዲናዋ የደንብ ጥሰቶችን በተሻለ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ ደንብ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የደንብ ጥሰቶችን በተሻለ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ አዲስ ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታወቀ።
በከተማ አስተዳደሩ የደንብ መተላለፍ በዓይነትና በቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ አዲስ የቁጥጥር ስልት ተግባራዊ ማድረግ ማስፈለጉ ታውቋል።
ለደንብ ማስከበር በችግርነት ከሚነሱት መካከል የህዝቡ ተሳትፎ ማነስ፣ የአንዳንድ ደንብ ተቆጣጣሪዎች የግንዛቤ ማነስና የስነ ምግባር መጓደል እንዲሁም የአንዳንድ አስፈፃሚ አካላት ጣልቃ ገብነት ይጠቀሳሉ።
የደንብ ጥሰት ሲያጋጥም በጊዜያዊነት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የችግሮቹ ምንጭ ላይ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት አለመስራት ሌላው ችግር መሆኑ ተገልጿል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ፉፋ÷ የደንብ መተላለፍ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት አዲስ የአሰራር ስርአት መዘርጋት ማስፈለጉን እና ለዚህም በሰው ኃይል እስከ ታችኛው እርከን በባለስልጣኑ አዲስ አደረጃጀት ተሰርቶ መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡
ይህም የደንብ መተላለፎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያግዛል ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ÷ ባለስልጣኑ የሚመራበት ደንብ በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ ለፍትህ ቢሮ መላኩን እና ደንቡን ተከትሎም መመሪያ እንደሚዘጋጅ አንስተዋል፡፡
የደንብ ማስከበር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመሆን ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በአዲስ መልክ የተዘጋጀው ደንብ ከዚህ በፊት የነበሩ የአሰራር ጉድለቶችን መነሻ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመሬት ወረራ፣ ህገ ወጥ ግንባታ፣የጎዳና ላይ ንግድን ጨምሮ ሌሎችንም ለመከላከልና ለመቆጣጠር የደንቡ መዘጋጀት ወሳኝ እንደሆነ አብራርተዋል።
የደንብ መተላለፍን በመከላከል ሂደት በተለይም የአንዳንድ አስፈፃሚ ግለሰቦች ጣልቃ ገብነት እንቅፋት እንደነበር እና በቀጣይ ማቆሚያ ሊበጅለት እንደሚገባ ማስገዘባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
Exit mobile version