የሀገር ውስጥ ዜና

ጃፓን በኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት እቅድ ትኩረት ለተሰጣቸው ዘርፎች ድጋፍ ለማድረግ እየሰራች ነው- አምባሳደር ኢቶ ታካኮ

By Feven Bishaw

May 28, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጃፓን በኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ትኩረት የተሰጣቸውን ዘርፎች በመለየት ድጋፍ ለማድረግ እየሰራች መሆኗን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ፡፡

ጃፓን የኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ እንዲሳካ ድጋፍ የምታደርግባቸውን ዘርፎች በሚመለከት ከመንግስት ጋር ውይይት እንደጀመረችም ነው የተናገሩት።

አምባሳደር ኢቶ ታካኮ እንደተናገሩት÷ የጃፓን መንግስት ከአምስት ዓመታት በፊት ለኢትዮጵያ ስለሚያደርገው ድጋፍ እቅድ ማውጣቱን ጠቅሰው፥ አሁን ላይ እቅዱን ማሻሻል የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያን ከ2013-2022 ዓ.ም የሚተገበር የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ነው ያነሱት፡፡

ጃፓን በእቅዱ ላይ የተቀመጡ የልማት ስራዎች እንዲሳኩ የበኩሏን ሚና ለመወጣት እንደምትሻ ገልጸው፥ አሁን የድጋፍ እቅዳችንን ከኢትዮጵያ የ10 ዓመት እቅድ ጋር ለማጣጣም እየሰራን ነው፤ በእቅድ ክለሳውም ቅድሚያ ትኩረት የምንሰጣቸውን ጉዳዮች እየለየን እንገኛለን ብለዋል።

ኢትዮጵያና ጃፓን የፖሊሲ ውይይት ሲያደርጉ ከስድስት ዓመታት ወዲህ የአሁኑ የመጀመሪያ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሯ፤ በቀጣይ ውይይቱ በየዓመቱ እንደሚካሄድ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አክለውም ኢትዮጵያና ጃፓን የንግድ ትብብራቸውን እያጠናከሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ቡና እና አበባን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ጃፓን እየላከች መሆኗን ተናግረዋል።

በቀጣይም ጃፓን አሁን ያለውን የንግድ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል።

አገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በተለይም በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በኤዥያ ፓስፊክ ትብብር ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ንዋያውን እንዲያወጡ እየተሰራ ስለመሆኑ የተናገሩት አምባሳደሯ፥ የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን በከፊል ወደግልዘ የማዞር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ የጃፓን የቴሌኮም ኩባንያ ገበያውን መቀላቀሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም መንግስት ለሳፋሪኮም ከሰጠው ድርሻ ውስጥ የጃፓኑ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን 27 በመቶ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።