አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተከናወኑ ሥራዎች 80 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ መሰጠቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ÷በክልሉ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በመጠቀም በተለያዩ ዘርፎች ባለሃብቶች እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው÷ባለፉት 9 ወራት በተደረገ ጥረትም 80 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 1 ሺህ 397 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን ጠቁመዋል።
ባለሃብቶቹ በወሰዱት ፈቃድ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ252 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ያነሱት ሃላፊው÷ ፈጥነው ሥራ እንዲጀምሩ አስፈላጊው እገዛ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ባለሃብቶቹ የኢንቨስትመንት ፍቃዱ የወሰዱት በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በሆቴል ቱሪዝምና መሰል ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ነው ተብሏል።
ባለፉት ዓመታት ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡ ከ3 ሺህ 600 የሚበልጡ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ75 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
በክልሉ አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች በ180 ኢንዱስትሪዎች ላይ ዝርፊያና ውድመት ማድረሱን ጠቁመው÷ በአሁኑ ወቅት 165ቱ መልሰው ተቋቁመው በከፊል ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው ÷ባለሃብቶችን ደግፎና ተከታትሎ ወደ ሥራ ለማስገባት ሁሉም ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡