ዓለምአቀፋዊ ዜና

የዓለም ባንክ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የ12 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው

By Meseret Demissu

March 04, 2020

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ባንክ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለሚደረገው ጥረት ለታዳጊ ሀገራት የ12 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው።

ድጋፉ አነስተኛ ወለድ ያለው ብድር፣ ልገሳና እና ቴክኒካዊ ድጋፍን ያካተተ ነው ተብሏል።

ተቋሙ ውሣኔውን ያሳለፈው ሃገራት የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ እየተንቀሳቀሱ ባለበት ወቅት ነው።

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ፥ ድጋፉ የቫይረሱን ስርጭትን ለመገደብ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም ቫይረሱ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም ድጋፉ ድሃና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሃገራት ቅድሚያ የሚሠጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም ባንክ ወረርሽኙ የሀገራትን ኢኮኖሚ በማቀዛቀዝ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ድጋፉ ሃገራት የወረርሽኙን ስርጭት መከላከል በሚያስችል መልኩ የጤና ስርዓታቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖን ለመቀነስ ያግዛል ነው የተባለው።

መነሻውን ቻይና ያደረገው የኮሮና ቫይረስ ዓለም ላይ ከ70 በላይ ሀገራት ማዳረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ምንጭ፡-ቢ.ቢ.ሲ