አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛን ዶክተር አኔት ዌበርን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና በሰሜኑ ግጭት እና በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየተደረገ ስላለው ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ለልዩ መልዕክተኛዋ ገለጻ አድርገዋል ።
መንግስት ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጎ እርዳታ እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።
በሰብአዊ እርዳታ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሰብአዊ እርዳታ እያሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል ።
በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀትም ሀገራዊ የምከክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱ፣ ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ በጦርነቱ እና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እንዲዳረስ የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት አውጆ እየተጓዘ ነው፤ በግጭቱ የተፈጠሩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ለመመርመር እና ተጠያቂ ለማድረግ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሰራም ነው ብለዋል።
አቶ ደመቀ ግብረ ኃይሉም አሁን ላይ 100 ባለሙያዎችን እንዳሰማራ ተናግረዋል ። መንግሥት የተፈጠሩ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ወቅት ግን የህወሓት የሽብር ቡድን ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ይህ የሽብር ቡድን አሁን ላይ በህዝብ ማዕበል ወደ ጦርነት ለመግባት የጥፋት ሴራውን እየነደፈ ነው ብለዋል ።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በህወሓት የሽብር ቡድን ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳርፍ ይገባል ነው ያሉት።
የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዶ/ር አኔት ዌበር በበኩላቸው መንግሥት ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ ያሳለፈው የተኩስ አቁም ውሳኔ እና ለችግሮች እልባት ለመስጠት እየተጓዘበት ያለው መንገድ አበረታች ነው ብለዋል ።
ልዩ መልዕክተኛዋ የአውሮፓ ህብረትም ለዚህ የመንግስት መልካም ጥረቶች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት ።
አቶ ደመቀ ከልዩ መልዕክተኛዋ ጋር በወቅታዊው የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ እና በህዳሴው ግድብ ዙሪያም ተወያይተዋል ።
በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶች በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ በውይይት ይፈታሉ ብለን እናምናለን፤ ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም አላት ብለዋል አቶ ደመቀ።
የአውሮፓ ህብረት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግጭቱ እና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።