አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የፓርኪንግ ብቃት ማረጋገጫ ከወሰዱ 214 የሕንፃ ስር የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት ሰጪዎች መካከል 74ቱ ወይም 34 ነጥብ 6 በመቶዎቹ ሕንፃዎች ከታለመለት ዓላማ ውጭ መዋላቸውን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የሕንፃ ስር ተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት ፈቃድ በወሰዱ 214 ተቋማት ላይ በኤጀንሲው የፓርኪንግ ልማት እና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በተካሄደ ድንገተኛ ምልከታ÷ 40 ነጥብ 2 በመቶ ያህሉ የሕንፃ ስር ተሽከርካሪ ማቆሚያውን ለታለመለት ዓላማ ማዋላቸው እና 34 ነጥብ 6 ሕንፃዎች ከታለመለት ዓለማ ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
25 ነጥብ 2 በመቶ ያህሉ ሕንጻዎች ደግሞ ለምን አላማ እንደዋሉ ማወቅ እንዳልተቻለ የኤጀንሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
የሕንፃ ስር ተሽከርካሪ ማቆሚያ ብቃት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው እና ምልከታ ተደርጎባቸው ለሌላ አገልግሎት ያዋሉ ተቋማት ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ኤጀንሲው ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡