የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ ባለይዞታዎች የይዞታ ይረጋገጥልኝ ማመልከቻ ማቅረቢያ ቀነ ገደብ ነገ እንደሚጠናቀቅ ኤጀንሲው ገለፀ

By Meseret Awoke

May 12, 2022

አዲስ አበባ፣ግንቦት 4፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በአዲስ አበባ ባለይዞታዎች የይዞታ ይረጋገጥልኝ ማመልከቻ በተሰጠው የጊዜ ገደብ እንዲያቀርቡ የከተማዋ የመሬት ይዞታ፣ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አሳሰበ፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ጀማል ሀጅ እንደገለፁት፥ ለይዞታ ማርጋገጫ በተመረጡ 25 ቀጠናዎች እና 112 ሰፈሮች የሚገኙ የመሬት ባለይዞታዎች የይዞታ ይረጋገጥልኝ ማመልከቻ እያቀረቡ ነው፡፡

ኤጅንሲው የይዞታ ይረጋገጥልኝ ማመልከቻ ሀሙስ ሚያዚያ 20 መቀበል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉት 6 ተከታታይ የስራ ቀናት ከ11 ሺህ 300 በላይ ባለይዞታዎች የይዞታ ይረጋገጥልኝ ማመለከቻዎችን ማቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡

የይዞታ ይረጋገጥልኝ ማመልከቻ የመቀበል ሂደቱ እስከ ግንቦት 5 ብቻ የሚቆይ በመሆኑ በተመረጡ ቀጠናዎች እና ሰፈሮች ውስጥ የሚገኙ ባለይዞታዎች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ መንጃ ፍቃድና አስፈላጊ መረጃዎችን በማሟላት የክፍለ ከተማ ቅ/ጽ/ቤቶች ባዘጋጁት ቦታ በመገኘት ማመልከቻ እንዲያቀርቡ ጥሪ አስተላልዋል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ ባለ ይዞታዎች ኤጀንሲው አረጋግጦ ላልመዘገበው ይዞታ ምንም ዓይነት ህጋዊ ዋስትናና ከለላ የማይሰጥ መሆኑን ተገንዝበው ቀነ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ሃላፊው አሳስበዋል፡፡

የይዞታ ይረጋገጥልኝ ማመልከቻ አቀራረቡንና አመዘጋገቡን ሂደት የሚታዘቡ ከህብረተሰቡ የተመረጡ 336 ታዛቢዎች እየተሳተፉ መሆናቸው ኤጅንሲው ለፋና ብሮድካስቲንግ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡