አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በባህር ዳር ከተማ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን በገመድ የተወጠረ ድልድይ የግንባታ ሁኔታ ጎብኝተዋል።
ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመት እና 43 ሜትር የጎን ስፋት አለው።
ወደ ድልድዩ የሚወስደው መንገድ ደግሞ 4 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፥ ግንባታዎቹ በመጪው ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ድልድዩ በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ማስተላለፍ የሚችል ባለሁለት አካፋይ ያለውና አምስት ሜትር የሳይክልና የእግረኞች መንገድ የሚያካትት ሲሆን፥ የትራፊክ ምልክቶች፣ የድልድይ ላይ መብራቶች፣ የተሽከርካሪ መውጫና ሌሎች የኮንክሪት መዋቅሮችንም የያዘ ነው።
የግንባታው አጠቃላይ ወጪም በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው።
አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 62 በመቶ ተጠናቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች የእውቅና እና የምስጋና መርሀ ግብር ላይ መገኘታቸው ይታወቃል፡፡