አዲስ አበባ፣የካቲት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ17 ዓመታት ያህል ጥሩ ጓደኛማቾች የነበሩት ቬኔዙዌላዊያኑ እህታማማቾች ሆነው መገኘት ግርምትን ፈጥሯል።
የ31 ዓመቷ አሽሊ ቶማስ እና የ29 ዓመቷ ቶያ ዊምበርሊ በፊላደልፊያ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሆነው መገናኘታቸውን ይናገራሉ።
ከዚህ ጊዜ በኋላም ሁለቱ ታዳጊዎች የማይነጣጠሉ የልብ ጓደኛማቾች ሆነዋል።
እነዚህ ጓደኛማቾችም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በበርካቶች ዘንድ ትመሳሰላላችሁ የሚል አስተያየት ሲደርሳቸው የነበረ ሲሆን÷ ከተወሰኑ ሰዎችም ዘንድም እህታማማቾች ናችሁ የሚል ጥያቄ ሲነሳላቸው ቆይተዋል።
ሆኖም እነዚህ ጓደኛማቾች በሚሰነዘረው አስተያየት እና ጥያቄ ሲስቁ እንደነበረ ያስታውሳሉ።
ነገር ግን አሽሊ ቶማስ የ15 ዓመት ታዳጊ እያለች ትክክለኛ ወላጅ አባቴ ብላ የምታውቀው አባቷ እንዳልሆነ ታረጋግጣለች።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም የ31 ዓመቷ አሽሊ ቶማስ እናቷን ትክክለኛ ወላጅ አባቷን እንድታሳውቃት ጥረት ስታደርግ ብትቆይም እናት የልጇን አባት ሳትናገር ከጥቂት ዓመታት በኋላ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።
በአንዱ ዕለት ግን ለ17 ዓመታት በጓደኝነት የዘለቁትን ሁለቱ ወጣቶች እህትማማቾች መሆናቸውን ሊያበስር የሚችል አጋጣሚ ይፈጠራል።
ይህም የአሽሊ ቶማስ ወላጅ እናት የቅርብ ጓደኛ በቅርቡ በፌስቡክ ላይ ዊምበርሊ የተሳፈችበት ፓርቲ ፎቶ ታገኛለች።
ከፎቶዎቹ ውስጥም የዊምበርሊ አባት ኬነዝ ዊምበርሊ ፎቶግራፎች መኖራቸውን ማየቷንና ይህ ሰው ደግሞ ከአሽሊ እናት ጋር ግንኙነት እንደነበረው ማስታወሷን ገልጻለች፡፡
ኬነዝ ዊምበርሊ የአሽሊን እናት እንደሚያስታውሳት የገለፀ ሲሆን÷ በዚህም የአሽሊ ወላጅ አባት ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬን ማደሩን አስታውሰዋል፡፡
የዲ ኤን ኤ ምርመራ ተደርጎም ጥርጣሬው እውን ሆኖ የአሽሊ ቶማስ ወላጅ አባት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ኬነዝ ዊምበርሊ በዜናው መደናገጡን ጠቁሞ÷ይህች ቆንጆ እና ስኬታማ ወጣት ሴት ልጄ በመሆኗ ተደስቻለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ሁለቱ ጓደኛማቾች እውነተኛ እህታማማቾች መሆናቸው መረጋገጡ ያላቸውን ግንኙነትና ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- www.upi.com