የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትየጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

By Meseret Awoke

May 10, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትየጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ዝርዝር ተግባራት ላይ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በባዮ ቴክኖሎጂ፣ በህዋ ሳይንስ እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ነው፡፡

እስከ 2025 በሚቆየው ይህ የትብብር ስምምነት የሰው ሃይል ስልጠና፣ የባለሙያ ልውውጥ፣ በኢኖቬሽን ሰታርትአፕ እና በሌሎች የሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት እንደሚያስችል ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

መሰከረም ወር ላይ የተቋቋመው የሁለቱ ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴ ያዘጋጀውን የትብብሩን ዝርዝር ተግባራት ሰምምነት በኢትየጵያ በኩል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ እና በደቡብ አፍሪካ በኩል ደግሞ የሳይንስና ኢኖቬሽን ዲፓርትመንት ተወካይ ዳን ዱ ቶይት ፈርመውታል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ፣ በምርምር እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ደቡብ አፍሪካ ያላትን የተሻለ ልምድ ኢትዮጵያ ትወስዳለችም ነው ያሉት፡፡

ሁለቱ ሀገራት በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ከዚህ በፊት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡