አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከዓለም ባንክ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አፈ ጉባኤው በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና የዓለም ባንክ ተወካይ በሆኑት ዶከተር ኡስማን ዲዎን የተመራ የልዑካን ቡድንን ነው በጽህፈት ቤታቸው ተቀበለው ያነጋገሩት፡፡
በውይይታቸውም ለልዑካን ቡድኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ሃላፊነትን በተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ÷ ባንኩ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያለቸውን እምነት ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ ተወካዩ ዶከተር ኡስማን ዲዎን በበኩላቸው÷ ምክር ቤቱ እያከናወነ ያለውን ስራ በማድነቅ በቀጣይም የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለመደገፍ እና አብሮ ለመስራት ፍላጎት ያላቸው መሆንኑን ገልጸዋል።
ዓለም ባንክ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በቅደም ተከተል የሚከናውኑ ተግባራትን ለመለየትና ለማቀድ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራዎች እንዲሰሩና የዓለም ባንክ ድጋፍም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደማይለይ አስታውቀዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በማስመልከት ምስጋና ማቅረባቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡