አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰራዊታችን እንደሀገር ሊቃጣብን የሚችልን ማንኛውም ትንኮሳና ጥቃት በብቃት መመከት በሚያስችል የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ተናገሩ።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከጀሌዎቹ ጋር በማበር የከፈተውን ሀገር የማፍረስ እቅድ መከላከያ ሰራዊታችን በውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ማክሸፍ መቻሉን ያስታወሱት ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና፥ ከዘመቻ በኋላ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ተቋሙ በሞራል፣ በሰው ኃይል ፣ በብቃትና በማቴሪያል የተሟላና ግዙፍ ኃይል እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ሰራዊታችን እያንዳንዷን ሰዓት በስልጠና ላይ በማዋል መቺና ድልን በአስተማማኝ መልኩ ማምጣት በሚችል ቁመና ላይ እንዲደርስ ማድረግ መቻሉን የገለፁት ጄነራሉ፥ ሀገራችንን ለመድፈር በሚያስቡ አካላት ላይ መንግስት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።
ተቋሙ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰራዊት የመገንባት ሂደቱን ያሳካና ሀገራዊ ፍቅርና ስሜት ያለው ሰራዊት የገነባ በመሆኑ ለቀጣይ የግዳጅ አፈፃፀም ስኬታማነት ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል ።
በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚነሳ እሳት እያንዳንዳችንን እንደሚጎዳ መረዳት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ጄነራል ጌታቸው ጉዲና ገልፀው፥ የተለያዩ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ ለጁንታውና አጋሮቹ ድጋፍ በመስጠት ሀገራችን አደጋ ላይ እንድትወድቅ የሚሰሩ አካላት ቆም ብለው ማሰብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።